Free Essay

Teshager

In: English and Literature

Submitted By teshager19
Words 522
Pages 3
ምሥራቀ ፀሐይ እመቤታችን
“እነሆም ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል ሉቃስ፤ምዕ.1ቁ48-49
ምሥራቀ ፀሐይ የሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህ
በነሐሴ ወር(በፆመ ፍልሰታ) በህጻናት በአዋቂዎች በአባቶች ካህናትና
እንዲሁም በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች በፆም
በጸሎት በስግደት በሰዓታት በኪዳንና በቅዳሴ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ
ሁኔታ ኃጢአታችንን እያሰብንና እያለቀስን ለአባቶቻችን ሐዋርያት
የተለመነችው እመቤት ለእኛም ትለመነን ታማልደን ከፈጣሪያችን ጋር
ታስታርቀን እያልን በትህትና ዝቅ ብለን የምንለማመንበትና ለሐዋርያት
የወረደው በረከት ለእኛም እንዲወርድልን ፍጹም የሆነውን ፍቅሯን
እንድታሳድርብን የምንማጸንበት ጊዜና ሰዓት ነው ለዚህ ደግሞ
በመብቃታችን በእውነት ዕድለኞች ነን።
እንግዲህ እኛም የእመቤታችንን ክብር ዘወትር ለመናገር አንደበታችን
ከቶውኑ አይደክምም ፈጥኖ ደራሽነቷን አበክረን እንመሰክራለን በረድኤት
ትታደገናለችና ምንጊዜም ቢሆን ንኢ ማርያም እያልን ስሟን እያጣፈጥን
እንጠራታለን ።
በዚህ የጾም ወቅት ስሟን እያጣፈጥን ብንናገር ብናወሳ ብንዘምር
ብንመሰክር በእውነት መላው ሰውነታችን ይታደሳል ቤታችን ሁሉ በበረከት
ይሞላል ልጆቻችን በሞገስ በጥበብ በዕውቀት እግዚአብሔርን እየፈሩ
አድገው ለሀገርም ለቤተክርስትያንም የሚጠቅሙ መልካም ፍሬዎች
ይሆናሉ
የእመቤታችን የደግነቷ ምስጢር ልዩ ነው ሰው ትወዳለች ታከብራለች
ፈጥናም ትደርሳለች የአዳም ዘር በሙሉ የቅድስተ ቅዱሳን የእመቤታችንን
ሥም እየጠራ ቢማፀናት ኖሮ ፈጥና ጸሎቱን ወደ እግዚአብሔር በማሳረግ
በርህርህና ዐይኖቿ ወደ ፍጥረቱ ሁሉ በመመልከት ምክንያተ ድሂን
መሆኗን ታሳየው ነበር። አዎን ማንም ሰው ከቁጥር እንዲጎድልባት
የማትፈልገው ምዕራገ ጸሎት የሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል
ማርያም ሳታቋርጥ ወደ ፈጣሪዋ ሁልጊዜ አበክራ ለእኛ ለኃጢአተኞች
እጆቿን ዘርግታ ምህረትን ትለምንልናለች።

በአልጋ ቁራኛ በደዌ ዳኛ የተያዙ ህሙማን እመቤታችንን እየተማፀኑ
ጠበሏ በፈለቀበት በተቀደሰው ቦታ ሁሉ ሄደው ከተያዙበት መጥፎ
የዲያብሎስ ቁራኛነት እየተላቀቁ የተመለሱና ለነፍሳቸው ያደሩ ብዙዎች
ናቸው።ለእምነታችን ጌጥ ለክርስትናችን ዕንቁ እንድትሆነን አምላክ የሰጠን
ከስጦታዎች ሁሉ ስጦታ የበለጠች ለነፍሳችን መንፈሳዊ እርካታን
የምናገኝባት ከመስቀሉ እግር ስር ያገኘናት ቅድስት እናታችን ናትና
አባቶቻችን እንዳመሰገኗት እኛም በዚህ በፍልሰታ ጾም አበክረን
እመቤታችንን ሳናቋርጥ ሰአሊ ለነ ቅድስት እያልን እንድናመሰግናት
አንደበት ትሁነን።
ማህደረ መለኮት እመቤታችንን ተስፋ አምባና መጠጊያ አድርገው
ከመጣባቸው የዲያብሎስ ፈተና በድል የተወጡ እንደ ሰማይ ኮከብና
እንደምድር አሸዋ ቁጥራቸው እጅግ የበዛ አያሌ ቅዱሳን አባቶችና እናቶች
በየዘመናቱ ይህን ዓለም ድል ነስተው በታላቅ ክብር ዘላለማዊ ሕይወትን
ወደሚያገኙበት መልካም ስፍራ ደስ እያላቸው አልፈዋል ይኼ ታዲያ
በዚህ ዘመን ላለን ኦርቶዶክሳውያን አማኞችና የእመቤታችን የቅድስት
ድንግል ማርያም ወዳጆች ለሆንን ሁሉ ከክብር ወደ ክብር የምንሸጋገርበት
ታላቅ የምስራች ነጋሪ ቃል ነው እላላሁ።
ከፍጥረታት ሁሉ የከበረች እመቤት ታላቅነቷን ነገደ መላእክት በሰማይ
የሰው ልጆችም በምድር ሆነው ንግሥተ ሰማይ ወምድር እያሉ ስሟን
በማጣፈጥ ሳያቋርጡ ይጠሯታል።
በከፋንና ተስፋ በቆረጥን ጊዜ ስንጠራት ሁሌ ልትረዳን የምትመጣው
እመቤታችን አስደናቂ ስራዋን በቃላት እንዲህ ነው ብለን የምንናገረው
ሳይሆን በእጹብነቱ ብቻ ግሩም ነው እንላለን።
ዓለም በጉስቊልና ጅራፍ እየገረፈች መላ አሳጥታን ውል ያለውን ነገር
እንዳናገኝ ከፊት እየቀደመች አበላሽታብን ነበርና ኦ! ወላዲተ አምላክ
እያልን ስንማጸናት በጸጋዋ ጎብኝታ በዘርፋፋው ቀሚሷ ከልላን ወደራሷ
ያስጠጋችን ጊዜ ቁጥሩ እጅግ ብዙ ነው።
ዲያብሎስ በተንሰራፋበትና በነገሰበት ዘመን እመቤታችንን ከጥፋት ሁሉ
የምታወጣ እውነተኛ አማላጅ ነች እያልን እንድንጠራት ያደረገን አምላክ
አቤት! ምን ያህል እድለኞች ብንሆን ነው?
በዚህ በጾም ወቅት ሁሉም እንደየማዕረጉ ከልጅ እስከ አዋቂ በለሆሳስ
በተመስጦ ዳዊቱን እየደገመ ኪዳኗን እያደረሰ ሁለንተናውን

ለእግዚአብሔር አስገዝቶ ፍጹም በሆነ መንፈሳዊ እርጋታ እየታቃኘ የልቤ
ማረፊያ ሲላት ወላዲተ አምላክ ምን ያህል ትደሰት ይሆን?
ማቅ ለብሰው ድንጋይ ተንተርሰው ቅጠል በልተውና ጥሬ ቆርጥመው በዱር
በገደል በበረሀ በዋሻ እራሳቸውን ለቅድስናና ለክብር አጭተው
እመቤታችንን መልዕልተ ፍጡራን መትህተ ፈጣሪ የምስራቅ በር አንቺ ነሽ
እያሉ ክብሯንና ጸጋዋን ሌትና ቀን እያደነቁና እያመሰገኑ ሲማጸኗት
መስማትና ማየት ለእኛና ለመጪው ትውልድ በበረከት በፍቅርና በሰላም
የመኖራችንን ምስጢር የሚያረጋግጡልንና የምስራችን የሚያበስሩልን
ተስፋዎቻችን ናቸውና እኛም ተምሳሌነቱን ይዘን እንድንጠቀምበት
እግዚአብሔር ይርዳን አሜን።የእመቤታችን አማላጅነት የቅዱሳን መላዕክት
ጠባቂነት የጻድቃን የሰማዕታት ተራዳኢነት ከሁላችን ጋር ይሁን አሜን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ከኃይለመስቀል ተስፋዬ
ነሐሴ 2006 ዓ/ም

Similar Documents